Healthy Food
The Healthy Fruits

የላቁ ምግቦች ለላቀ ጤና

የትኛው ፍራፍሬ ነው የደም ግፊትዎን ለመቀነስ የሚረዳዎት? ለምንድነው ሎሚ የጤና ግምጃ ቤት (ሱፐር ሃውስ) የሆነው? የኦሜጋ-3 እጥረት እንዴት ከድባቴና (ድብርት) ከአንዳንድ አካላዊ ችግሮች ጋር ይያያዛል? በየዕለቱ ከምንመገባቸው ምግቦች እነዚህን ጠቃሚ ኦሜጋ -3 ፋቲ አሲዶች ከየትኞቹ ምግቦች እናገኛለን? ለዓይንዎ ብርሃን ይጨነቃሉ? እንግዲያውስ የትኞቹ የላቁ ምግቦች (ሱፐር ፉድ) እንደሚረዱዎት ከዚህ ጽሑፍ ያገኛሉ፡፡ 
1. ሰማያዊ አጋም (Blue berries):- እነዚህ በግሩም ጣዕምና መዓዛ የተሞሉ ሰማያዊ የአጋም ፍሬዎች፣ ተፈጥሮ ከፍተኛ የመድኃኒትነት ፀጋ ከቸረቻቸው ምግቦች አንዱ ናቸው፡፡ ባክቴሪያዎች፣ ወደ ሽንት መተላለፊያ ቧንቧ ገብተው በመመረዝ፣ የሽንት መተላለፊያ አካባቢ ምርቀዛ (ዩሪናሪ ትራክት ኢንፌክሽን) እንዳይፈጠር መተላለፊያውን በመዝጋት የፀረ – ባክቴሪያ (አንቲባዮቲክ) ሚና ይጫወታሉ። አንዳንድ ሰዎች እነዚህን ፍሬዎች አቀዝቅዘው መብላት ይፈልጋሉ፡፡ ለምን መሰላችሁ? ቀዝቅዘው ሲበሉ፣ ተበጥብጠው እንደሚጠጡ ጣፋጭ ነገሮች (Sherbet) ጣዕም ስለሚኖራቸው ነው፡፡
እነዚህ በቫይታሚን ሲ፣ አሰርና (fiber) በብረት ማዕድናት የበለፀጉ ፍሬዎች፣ የሰውነትን ሕዋሳት (ሴሎች) በመጉዳት እርጅና የሚያፋጥኑትን ፋቲ አሲድ የተባሉት መጥፎ ኬሚካሎች፣ የጉዳት ኃይላቸው እንዲለዝብ (neutralize) በማድረግ ባላቸው ችሎታ፣ 40 ዓይነት አትክልትና ፍራፍሬ ያስከነዳሉ፡፡ ጥቅማቸው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ለዓይን እይታም ይረዳሉ፡፡ 
በዚህ ይዘታቸው የተነሳ፣ ጃፓኖች፣ “የእይታ ፍሬ” (Vision fruit) በማለት ያሞካሿቸዋል። እርስዎ ምን ይጠብቃሉ? የገጠር ልጅ ከሆኑ ከብቶች ሲያግዱ ከየቁጥቋጦ ውስጥ አጋሞ ሳይበሉ እንዳልቀሩ እገምታለሁ። ስለዚህ አገር ቤት ያሉ ዘመዶችዎ እንዲያመጡልዎት ይማፀኑ፡፡ ሌላው አማራጭ በእርሻ ዘርፍ የተሠማሩ ኢንቨስተሮች አጋም አምርተው በየሱፐርማርኬቱ ቢያቀርቡ እኛም እነሱም እንጠቀማለን፡፡ 
2. አቮካዶ፡- ይህ ምግብ “የተፈጥሮ ቅቤ” በመባል ነው የሚታወቀው፡፡ አቮካዶ፣ በተለያዩ ጐጂ የቅባት ዓይነቶች (የእንስሳት ቅቤ፣ ጮማ…) የተሞላና የታጨቀ (Saturated) አይደለም፡፡ አቮካዶ የያዘው ቅባት አንድ ወይም ነጠላ (Monosaturated) ነው። ስለዚህ በምግብ ሳይንቲስቶችና ባለሙያዎች ዘንድ እንደ “ጥሩ” ቅባት ነው የሚታየው፡፡ በመሆኑም በልብ በሽታ የመያዝ ስጋትን እንደሚያስቀር ይታመናል፡፡ 
ታይሮይድ ዕጢ ችግር እንዳይፈጠር ከመከላከሉም በላይ፣ ቆዳን ለማሻሻል በጣም ጥሩ የሆነው የቫይታሚን ኢ ከፍተኛ መገኛ ነው። አንዳንድ ጥናቶች አቮካዶ፣ የእጅ፣ የወገብ፣ የጉልበትና የእግር መገጣጠሚያዎችን በማሳበጥ ሕመም የሚፈጥረውን Rheumatoid arthritis የተባለ በሽታ ለመከላከል እንደሚረዳ አመልክተዋል፡፡ ሌላው የአቮካዶ ጥቅም ደግሞ፣ ሉቴይን (Lutein) የተባለ ኃይለኛ ፀረ – ኦክሲደንት (ኦክሲደንት፣ ኦክሲጅን ከሌላ ነገር ጋር ሲገናኝ የሚፈጠር ነገር ወይም ዝቃጭ ማለት ነው) ስላለው፣ ዓይኖችን ካተራክትስ ከተባለ በሽታ ይከላከላል፣ የደም ስሮች እንዳይደድሩ (እንዳይጠነክሩ) ያደርጋል። አቮካዶ መብላት ወይም ጭማቂውን መጠጣት ጥሩ አይደለም ታዲያ!
 3. ሙዝ፡-  ይህን ጽሑፍ ያነበቡ ነጋዴዎች ጥቅሙን አውቀው ዋጋ እንዳይሰቅሉብን እንጂ፣ ሙዝ፣ በጣም ጠቃሚ ምግብ ነው፡፡ ጥቅሙን፣ እኛ ብቻ ሳንሆን ዝንጀሮችም አሳምረው ያውቁታል፡፡ ሙዝ ሲበሉ ፈጥነው ጉልበት (ኃይል) ከማግኘታቸውም በላይ፣ ተወዳጁ ምግባቸው ማግኒዝየም የተባለውን ማዕድንና B6 የተባለውን ቫይታሚን ያስገኝላቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳ በምድር ወገብ አካባቢ፣ እጅግ ጠቃሚ የምግብ ይዘት ካላቸው ፍራፍሬዎች አንዱ መሆን ችሏል፡፡ 
ባልበሰለ አረንጓዴ ሙዝ ውስጥ ያለው አሰር (ፋይበር) መጥፎ ኮሌስትሮልን ይቀንሳል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሙዝ መብላት ለሆድ ሕመም ይደርጋል ሲሉ ይደመጣል፡፡ እውነቱ ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ሆድ ሲጐረብጥ፣ መፍትሔው፣ የበሰለ ሙዝ መብላት ነው። ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ምግብ አልፈጭ ብሎት ቃር (ሄርት በርን) ሲሰማዎት ሙዝ ቢበሉ እፎይታ ያገኛሉ፡፡ 
ሙዝ፣ ስትሮክ በተባለ በሽታ የመያዝ ስጋትንም ይቀንሳል፡፡ የደም ግፊትን በሚቀንሰው ፖታሲየም የተባለ ማዕድንም የተሞላ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ጥቅሞቹ የተነሳ ሙዝ፣ የላቀ የጤና ምግብ መባሉ የሚበዛበት አይመስለኝም፡፡ 
4. ነጭሽንኩርት፡- ይህ የቅመም ምግብ ያለውን ጥቅም የማያውቅ ሰው የለም ማለት ይቻላል። “የሚሰነፍጠው ኃይለኛ ጠረኑ አስቸገረን እንጂ ጥቅሙማ መች ጠፋን?” እንደምትሉ እገምታለሁ፡፡ እንግዲህ ክረምቱ ገባ አይደል? በዚህ ወቅት ደግሞ ጉንፋኑ፣ ኢንፉሌንዛው፣ ይበረታል፡፡ መድኃኒቱ ደግሞ ነጭ ሽንኩርት ነው፡፡ 
ለዚህ የነጭ ሽንኩርት መጥፎ ጠረን መላ ሲያፈላልጉ የነበሩት የምግብ ሳይንቲስቶች ምስጋና ይግባቸውና ጥረትና ድካማቸው የሰመረላቸው ይመስላል፡፡ ለነጭ ሽንኩርት መጥፎ ጠረን አገኘን ያሉትን መፍትሔ፣ ባለፈው ኤፕሪል ወር በፖሉላር መጽሄት ላይ አቅርበዋል። 
ሳይንቲስቶች መፍትሔ ነው ያሉት ዘዴ በዚሁ ገጽ ቀርቧልና ይሞክሩት፡፡ አሁን ወደተነሳንበት የነጭ ሽንኩርት ጥቅም ትንታኔ እንመለስ፡፡ 
አንዳንዶች በተለምዶ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ነጭ ሽንኩርት መልካም ዕድል ይፈጥራል፣ መጋኛ፣ ሸረኛ፣ ቡዳ፣ መተተኛ፣ ጥንቆላ፣ በሌሊት ከመቃብራቸው እየወጡ የሰው ደም ከሚመጡ የሙታን ነፍሶች (ቫምፓየር)፣ …ከመሳሰሉ እርኩስ መናፍስት ይከላከላል፣ ያርቃል፣ የሚል እምነት አላቸው፡፡ 
እውነቱ ግን፣ ነጭ ሽንኩርት “የቅመሞች ንጉሥ” (King of the herbs) የሚለው ቁልምጫና ቅጽል፣ የሚገባው መሆኑ ነው፡፡ ትኩስ የተፈጨ ነጭ ሽንኩርት፣ በጠረኑ ብቻ 20 ሳ.ሜ ርቀት ላይ ያለ ቫክቴሪያ ይገድላል፡፡ ይህ ቅመም፣ ለበሽታ መከላከያ አቅም ግንባታ፣ ለምግብ መፈጨት፣ ለነርቭ ሲስተም፣ ለመተንፈሻና ለቆሻሻ ማስወገጃ ሲስተም ይረዳል፡፡ እንዲሁም፣ ለልብ፣ ለሳንባ፣ ለፀጉርና ለዓይን ጤንነት በጣም ጥሩ ጥቅም ይሰጣል፡፡ 
ነጭ ሽንኩርት የበሽታ መከላከያ አቅምን ከፍ የሚያደርገው፣ አሊሲን (allicen) በተባለው ፈጣን ንጥረ ቅመሙ (ingredient)  አማካይነት ነው፡፡ አንዳንድ ጥናች ደግሞ ነጭ ሽንኩርትን ከሆድ ካንሰር መቀነስ ጋር አያይዘውታል፡፡ ጉንፋን ወይም ኃይለኛው የጉንፋን ወረርሽን (ፍሉ) ሲይዝ ነጭ ሽንኩርት መብላት (መጠቀም) የበሽታውን የመቆያ ጊዜ በግማሽ ይቀንሳል፡፡ ምን ይኼ ብቻ? የነጭ ሽንኩርት ጥቅም በርካታ ስለሆነ፣ ከገበታዎ እንዳይጠፋ ካደረጉ ዘየዱ ማለት ነው፡፡ ጥሬውን ቢበላ ግን ይመረጣል፡፡    
5. Pomegranates:- ይህ ፍሬው የሚበላና የላቀ የመድኃኒትነት ይዘት ያለው ምግብ፣ ከቀይ ወይንና ከአረንጓዴ ሻይ የበለጠ ከፍተኛ ፀረ – ኦክሲደንት (አንቲ ኦክሲደንት) አቅም አለው። በዚህም የተነሳ፣ ይህ ፍራፍሬ፣ የቆዳ ካንሰር እንደሚከላከል፣ የጡትና የወንድ ዘር መተላለፊያ ቧንቧ (ፕሮስቴት) የሚያጠቃውን የካንሰር ሕዋሳት (ሴሎች) እንደሚገድል በርካታ ጥናቶች አሳይተዋል።   
ይህ ፍራፍሬ፣ አልዛሂመር የተባለውን የመርሳት በሽታ ለመዋጋት ይረዳል፡፡ እንዲሁም፣ በደም ስር (አርቴሪቲስ) ውስጥ የደምን ዝውውር የሚያውኩ ነገሮች (Plaque) እንዳይፈጠሩ ያደርጋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የአንጀት ተግባርን ያቀላጥፋል፣ ለቆዳ ምግብ የሚያቀብሉ በጣም ደቃቅ የደም ስሮች ግድግዳን ያጠነክራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኃይለኛ የወሲብ ስሜት ቀስቃሽ መሆኑ በስፋት እየተሞገሰ ነው፡፡ ምን ዓይነት ሁሉን አቀፍ ምግብ ነው!!
6. ቲማቲም:- የዚህ ቀላ ያሉ ፍሬዎች ጭማቂ፣ ከካንሰርና ከልብ በሽታ የሚከላከል፣ የኮሌስትሮል መጠን የሚቀንስ ላይኮፔን (Lycopen)  የተባለ ፀረ – ኦክሲደንት ይዟል፡፡ ላይኮፔን፣ ከቀይ ቃሪያና ከሀባብ (watermelons) የሚገኝ ሲሆን፣ ከጥቂት ዘይት ጋር ሲወስድ፣ ከሰውነት ጋር በቀላሉ ይዋሃዳል፡፡ በአጠቃላይ፣ ለመልካም ጤና፣ በቀን ቢያንስ አንድ የተቀቀለ ቲማቲም ይብሉ፡፡ በቲማቲም ሱጐ (ሶስ) የተሠራ ፓስታ ወይም ፒዛ፣ መብላትም ተመሳሳይ ውጤት ያስገኛል፡፡ 
7. ዓሳ:-  እንደ ቱና፣ ሳልሞን፣ ሰርዲን፣ መክሬል፣ ሂሪንግስ፣…የመሳሰሉ ዘይታማ ዓሳዎች፣ ኦሜጋ – 3 በተባለ በጣም አስፈላጊ ስባማ (ፋቲ) አሲድ የበለፀጉ ናቸው፡፡ እነዚህ ፋቲ አሲዶች፣ ለአንጐልና ለሰውነት ዕድገት እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ እነዚህ ጠቃሚ ፋቲ አሲዶች፣ በስትሮክ፣ በልብ በሽታ፣ በአንዳንድ ካንሰሮችና አልዛሂመር በተባለ የመርሳት በሽታ የመያዝ ስጋትን እንደሚቀንሱ ተረጋግጧል፡፡ 
የኦሜጋ-3 እጦት፣ የደስታ ስሜትን ይቀንሳል፤ ድባቴ (ድብርት) ይፈጥራል፣ የተለያዩ የአዕምሮና የአካል ችግሮችን ያስተካክላል፡፡ ዓሳ አይወዱም? ምንም ችግር የለም፡፡ አስፈላጊውን ኦሜጋ-3 ከተለያዩ ምግቦች ማግኘት ይችላሉ፡፡ በየቀኑ flaxseeds (linseed)፣ walnuts, rapeseed oil, seaweed, spirulina, watercress, ወይም የኦሜጋ – 3 ተጨማሪ ተብሎ ከሚታዘዝ መድኃኒት ማግኘት ይቻላል፡፡ 
8. ሻይ፡- በእርግጥ ሻይ ጥምን ከማርካትም በላይ በጣም የሚጥም ነው፡፡ ነገር ግን ሻይ ከምግብነትም አልፎ በሽታ የመከላከል አቅም እንዳለው በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች አሳይተዋል፡፡ ሻይ ከፍተኛ ጸረ-ኦኢክሲደንት ስላለው ካንሰርና የልብ በሽታን ይከላከላል፡፡ ነገር ግን፣ ሻይ ውስጥ ወተት ወይም ይባስ ብሎ ስኳር ከተጨመረበት፣ ለጤና የሚሰጠውን ጥቅም ያጣል፡፡ 
ኃይለኛ የሻይ ሱሰኞች የሆኑ ሰዎች፣ በየቀኑ በእያንዳንዱ ብርጭቆ ወይም ሲኒ የሚጨምሩት በጣም ጥቂት ወተት ሲደመር፣ በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኘውን ስብ ሲያክል የፀረ ኦክሲደንቱ የመከላከል አቅም ስለሚቀንስ በልብ በሽታ የመያዝ ስጋት ይጨምራል፡፡ ስለዚህ የተጠቀሰውን ጥቅም ለማግኘት ከፈለጉ ሻይ ውስጥ ምንም ሳይጨምሩ ባዶውን ይጠጡ – እንደ እንግሊዞች፡፡
9. ሎሚ፡- ይህ የተለያዩ ከፍተኛ ጥቅሞች የያዘው ወርቃማ ፍሬ፣ እውነትም የዓለማችን የጤና ማዕከል (power house of health) ነው፡፡ ሎሚ፣ ሰውነታችን የሚፈልጋቸውን ቫይታሚኖችና ማዕድናት ይዟል፡፡ ለምሳሌ፣ የቫይታሚን ቢ እና ኢ መገኛ ነው፡፡ ፖታሲየም፣ ማግኒዚየም፣ ኮፐር (መዳብ)፣ ፎስፈረስ፣ ዚንክ፣ ብረት፣ ማንጋኒዝ ይዟል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የቫይታሚን ሲ ከፍተኛ ምንጭ ነው፡፡ 
ሎሚ፣ ለምግብ ስልቀጣ መስመር፣ ለመተንፈሻ ሲስተም፣ ለልብና ለደም ዝውውር በጣም ጠቃሚ በሆነው ባዮፍላቮኖይድስ (bioflavonoids) የተሞላ ነው፡፡ ሎሚ፣ የቆዳና የሰውነት ህብረ ህዋሳት (ሌሎች) ጤናማ ሆነው እንዲቆዩ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ በትኩሱ፣ በጥሬው ወይም በፈሳሽ መልክ መወሰድ አለበት፡፡ 
10. ወይን፡- የወይን ፍሬዎች፣ ፀረ-ካንሰር ይዘት ባለው ባዮፍለቮኖይድስ የበለፀጉ ናቸው፡፡ እነዚህ የሐረግ ፍሬዎች፣ የካንሰር ሴሎችን ዕድገት የሚያነቃቃውን ኤንዛይም የሚገድል ረስቨራትሮል (resrveratrol) የተባለ ኬሚካል አላቸው፡፡ ኬሚካሉ የደም ስሮችን መጥበብና መደደር ይከላከላል፡፡ 
ይህ አልበቃ ብሏቸው የወይን ፍሬዎች በአሰርና (ፋይበር) ፕሮቲን የተሞሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ በሳምንት አምስት ጊዜ ጥቂት የወይን ፍሬዎች ይብሉ ወይም ጨምቀው ይጠጡ፡፡ የዓይን ብርሃን ስጋት አለብዎት? እንግዲያውስ ቀይ ወይን ፍሬ ይብሉ፡፡ ምክንያቱም ቀይ ወይን ከዕድሜ መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የዓይን ጡንቻ እርጅና የሚከላከኩት ካሮቴኖይድ ሊቴይንና (carotenoids lutein) ዘዛንቲን (Zeaxanthin) መገኛ መሆናቸው በጥናት ተረጋግጧል፡፡ 
11. ብሮኮሊ፡- ለተደጋጋሚ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች፣ ብሮኮሊን ‹አስገራሚ ምግብ› ብለውታል፡፡ ይህ የአበባ ጎመን ፍሬ የመሰለ አረንጓዴ ፍሬ ነገር ከብስቴክ በእጥፍ የበለጠ ፕሮቲን አለው፡፡ እንዲሁም በርካታ ካንስሮችን፣ አልዛሂመር የተባለውን የመርሳት በሽታና የተቀሩትን አደገኛ በሽታዎች ለመከላከል የሚረዳው ፎሊክ አሲድ መገኛ ነው፡፡ 
ብሮኮሊ፣ በክሮሚየምና ብረት ማዕድናት፣ በቫይታሚን ሲ የበለፀገ ከመሆኑም በላይ የፊንጢጣ ካንሰር እንዳይፈጠር በሚከላከል ከፍተኛ የአሰር መጠን (ፋይበር) የተሞላ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ አረንጓዴ ነገሮች ለጤናም አሰፈላጊ ስለሆኑ በሳምንት ሶስት ጊዜ ለመብላት ያቅዱ፡፡
ምንጭ፡- ሰላምታ መጽሔት July – September 2011 

Source

– Via : Addisadmassnews.com

Original Link
http://www.addisadmassnews.com/index.php?option=com_k2&view=item&id=14446:%E1%8B%A8%E1%88%8B%E1%89%81-%E1%88%9D%E1%8C%8D%E1%89%A6%E1%89%BD-%E1%88%88%E1%88%8B%E1%89%80-%E1%8C%A4%E1%8A%93&Itemid=233