aLEXANDER pUSHKIN
ሩሲያ የፑሽኪን ሐውልትን ለኢትዮጵያ ልታስረክብ ነው

ሩሲያ የፑሽኪን ሐውልትን ለኢትዮጵያ ልታስረክብ ነው

የሩሲያው ገጣሚ አሌክሳንደር ሰርገየቪች ፑሽኪን ሐውልት ከሞስኮ ወደ አዲስ አበባ ሊዘዋወር ነው፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ የታሪክ ባለሙያዎች የኤርትራን መገንጠል ተከትሎ የፑሽኪን ማንነት ላይ የማይግባቡ ቢሆንም፤ የሥነ ጽሑፍ ጥበብን በሩሲያ የፈነጠቀውን የታዋቂው ጥቁር ገጣሚ አሌክሳንደር ፑሽኪንን ሐውልት በቅርቡ ለአዲስ አበባ ልታስረክብ ነው፡፡

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ በተገኙበት ወቅት ከኢትዮጵያ መንግሥት ሹማምንት ጋር በዚሁ ጉዳይ ተነጋግረው መግባባታቸውንና ሐውልቱ ለአዲስ አበባ ከተማ የሚተላለፍበት መንገድን ለማፋጠን እንደሚሠሩ ሚኒስትሩ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ባለፈው ረቡዕ ገልጸዋል፡፡

ፑሽኪን የተወለደው በሞስኮ ከተማ በግንቦት 18 ቀን 1791 ዓ.ም. መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ፑሽኪን በእናቱ በኩል የሚመዘዘው የዘር ሐረጉ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ይገባል፡፡ አያቱ አብርሃም አኒባል ኢትዮጵያ ተወልደው የኖሩና በባርነት ወደ ሩሲያ የተጓዙ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ አያቱ ተወልደው ያደጉበት አንዳንዶች ደግሞ ፑሽኪን ራሱ ተወልዶበታል የሚሉት አካባቢ ሎጐ ጎርዳ የኢትዮጵያ ግዛት ነበረች፡፡ ይሁን እንጂ የኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል ተከትሎ ፑሽኪን ኤርትራዊ የዘር ሐረግ ያለው ነው የሚል ክርክር ይደመጣል፡፡ በ1994 ዓ.ም. ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ላይ የፑሽኪንን ከአንገት በላይ ሐውልት በመቅረጽ አደባባይና ጐዳና መሰየሟ ይታወቃል፡፡ ኤርትራ ደግሞ ከሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ በተመሳሳይ የፑሽኪንን ሐውልት ቀርፃ አደባባይ ሰይማለች፡፡ ሁለቱም አገሮች ሐውልቱን ሲያስመርቁ የሩሲያ ዲፕሎማቶች መገኘታቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

በሩሲያ አገር የተማሪነት ዘመናቸው ከአገሪቱ ባህልና አኗኗር ጋር የተዋወቁት ብሎም የፑሽኪንን የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች ወደ አማርኛ በመመለስ የሚታወቁት ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ የዝነኛው ገጣሚ ሐውልት ለኢትዮጵያ መበርከቱ ትልቅ ክብር ነው ይላሉ፡፡

‹‹ፑሽኪን ማነው? በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ የኪነ ጥበብ ሰው ነው፣ ከነሼክስፒርና ሌሎች የአውሮፓ ታላላቅ ደራስያን ጋር የሚጠራ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እ.ኤ.አ. 2000 ላይ የፑሽኪን ዘመን ብሎ የዘከረለት ታላቅ ሰው ሐውልት ለኢትዮጵያ ተበረከተ ማለት ክብር ነው›› ብለዋል፡፡

ፑሽኪን ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያምን እንደነበር የሚናገሩት አቶ አያልነህ የሐውልቱ መምጣት የሁለቱ አገሮችን ጥንታዊ ወዳጅነት የበለጠ የሚያስተሳስር ነው ብለዋል፡፡

SOURCE
-BY :  ዮሐንስ አንበርብር
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/life-and-art/item/7462-%E1%88%A9%E1%88%B2%E1%8B%AB-%E1%8B%A8%E1%8D%91%E1%88%BD%E1%8A%AA%E1%8A%95-%E1%88%90%E1%8B%8D%E1%88%8D%E1%89%B5%E1%8A%95-%E1%88%88%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB-%E1%88%8D%E1%89%B3%E1%88%B5%E1%88%A8%E1%8A%AD%E1%89%A5-%E1%8A%90%E1%8B%8D