የአበበ ቢቂላ የቶኪዮ ድል ወርቃዊ ኢዮቤልዩ
Aebe Bikela

የአበበ ቢቂላ የቶኪዮ ድል ወርቃዊ ኢዮቤልዩ

-ታሪክና አፈ ታሪክ በገድለ አበበ ቢቂላ

‹‹አበበ ቢቂላ በጳጉሜን 1952 ዓ.ም. የሮም ኦሊምፒክ ማራቶን በባዶ እግሩ ሮጦ ተአምራዊ አሸናፊ ከሆነ ወዲህ የማራቶንን ሩጫ በ2 ሰዓት ከ14 ደቂቃ የሚጨርስ ቢኖር ሻምፒዮን ይባላል፤ በ2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ የሚፈጽም ከተገኘ ደግሞ ድንቅ ሻምፒዮን ይባላል፡፡

አበበ ቢቂላ ግን በቶኪዮ ኦሊምፒክ 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ11.2 ሰከንድ በማምጣቱ ምን ብዬ እንደምለው ቃላት አጥቼለታለሁ፡፡››

ከ50 ዓመት በፊት አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ጊዜ ታላቁን ሩጫ ማራቶንን አሸንፎ ወርቅ ሲያጠልቅ ‹‹የበርሊን ማራቶን መጽሔት›› ዘጋቢ የጻፈው ነው፡፡

ረቡዕ ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም. ነበር፤ ቦታው ጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ በተለይ 15 አትሌቶች የኦሊምፒኩን የወርቅ ሜዳሊያ ለማግኘት ቋምጠዋል፤ ለመፎካከር አፍጥጠዋል፡፡ የሮሙ ባለወርቅ አበበ ቢቂላ የትርፍ አንጀት ቀዶ ሕክምና ማድረጉና ሳያገግምም ከውድድር ሥፍራ መድረሱም የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ካልሲ አጥልቆ፣ ጫማውን ለተጫማው አበበ ውድድሩ አስቸጋሪ አልሆነበትም፡፡ እስከ መጀመሪያዎቹ 10 ኪሎ ሜትር የአውስትራሊያው ሮን ክለርክ ቢፎካከረውም ጥሎት በመሔድ ያለአንዳች የቅርብ ተቀናቃኝ በ2 ሰዓት 12 ደቂቃ 11.2 ሰኮንድ በድል አድራጊነት ፈጸመ፡፡ ከእርሱ በፊት ማንም ያልፈጸመውን፣ ከርሱም በኋላ ለ16 ዓመታት ማንም ያላደረገውን የኦሊምፒክ ማራቶን ሁለት ጊዜ አከታትሎ የመውሰድ ገድል ፈጸመ፡፡ ይኸም ብቻ አይደለም ባሸናፊነት የገባበት ሰዓትም እጅግ በጣም ፈጣንና በእንግሊዛዊው ባሲል ሔትሌይ በ2 ሰዓት 13 ደቂቃ 55 ሰኮንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን በ1 ደቂቃ 43 ካልዒት (ሰከንድ)፣ 8 ሣልሲት (ማይክሮ ሰከንድ) የሰበረበት ነው፡

‹‹እንደ በረዶ ነጫጭ ጥርስ አብቅሎ 

ይቆረጣጥማል ሰዓት እንደቆሎ›› ብለው በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ (1914-1979) እንዲቀኙለት አድርጓቸዋል፡፡

አበበ በቶኪዮ ማራቶን ከመወዳደሩ 36 ቀናት በፊት ረቡዕ መስከረም 6 ቀን 1957 ዓ.ም. ቀዶ ሕክምና አድርጎ ስለነበር እንኳን ሊያሸንፍ ውድድሩን ይፈጽማል ብሎ ያሰበ አንድም ሰው አልነበረም፡፡ 70,000 የሚሆነው የቶኪዮ ስታዲየም ተመልካች ማን ያሸንፍ ይሆን? እያለ ውድድሩን በጉጉት ሲጠባበቅ ማሸነፍን ምሱ ያደረገው ሸንቃጣው አበበ የ30 ደቂቃ የሰውነት ማሟሟቂያ አድርጎ ከመናፈሻ እንደወጣ አትሌት እየተዝናና ከስታዲየሙ ሲደርስ ተመልካቹ ዓይኑን ማመን አቅቶት ነበር፤ ከዚያም ውድድሩን አጠናቆ ወዲያውኑ እንደ ጠዋት የ5 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጅምናስቲክ መሥራት ሲጀምር ተመልካቹ መጀመሪያ ፈገግ አለ፡፡ ከዚያም በመገረም ዘግየት ብሎ አድናቆቱን በከፍተኛ ጭብጨባ ገለጸለት፤ ይላል ገድሉን የዘገበው የባሕር ማዶ መጽሔት፡፡

ዴቪድ ዋልቺንስኪ በኦሊምፒክ ድርሳኑ (The Complete History of Olympics 2004 Edition) እንደጻፈው፣ አበበ አካሉን ሲያፍታታ ላየው ‹‹አዝናለሁ፣ ማራቶን አጭር ሆኖብኛል›› ያለ አስመስሎበታል፡፡ እንዲያውም ለጋዜጠኞች በዚያን ጊዜ በሰጠው ምላሽ ለሌላ 10 ኪሎ ሜትር የሚያስሮጠኝ ኃይል አለኝ ነበር ያላቸው፡፡

በሜዳሊያ ሽልማት ሥነ ሥርዓቱም አንድ ያልተጠበቀ፣ ከዚያም በፊትም ያልታየ ሌላ አስደናቂ ነገር ተከሰተ፡፡ አበበ ቢቂላ በሮም እንዲሁም ከቶኪዮ በኋላ ማሞ ወልዴ በሜክሲኮ (1961 ዓ.ም.) ማራቶንን ሲያሸንፉ የተዘመረላቸው

‹‹ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ፣ 

ባምላክሽ ኃይል በንጉሥሽ›› የሚለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር የጃፓን ባለሥልጣኖችም ሆኑ የሙዚቃ ባንዱ አያውቁትም ነበር፡፡ እናም ዘየዱ፤ የማርሽ ባንዱ አጋጣሚውን ተጠቀመ፡፡ የጃፓንን ሕዝብ መዝሙር ለኢትዮጵያ ድል ማብሰሪያ አደረገው፤ ሕዝቡም ፈነደቀ፡፡ 17 ቁጥር መለያን ያጠለቀው አበበም በጃፓን ሕዝብ ልቡና ውስጥ ታተመ፡፡ ነፍስኄር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ከአራት አሠርታት በፊት እንዳሉት፣ ‹‹…አበበ በድጋሚ በማሸነፉ በጃፓን ሕዝብ ለዘለዓለም የማይረሳ ትዝታ ትቷል፡፡ ዛሬም በጃፓን እንደጣዖት ይመለከቱታል፡፡ ማራቶን በጃፓን ውስጥ እንዲህ ተወዳጅ ሊሆን የቻለው ከአበበ ቢቂላ ድል በኋላ ነው፡፡ አሁንም ይኸው መንፈስ ቀጥሏል፡፡››

ጃፓናውያን ለአበበ ክብር በቀዬያቸው ሐውልት አቁመውለታል፡፡ አምና በጥር ወር አዲስ አበባ ጎራ ያሉት የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በ1957 ዓ.ም. በተካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ በማራቶን ድል ያደረገውን አበበ ቢቂላ ለማክበር ከልጁ ከየትናየት አበበ ቢቂላ ጋር በሸራተን አዲስ ጥር 5 ቀን 2006 ዓ.ም. ተገናኝተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር  አቤ የቶኪዮውን ሩጫ በልጅነታቸው እንደተመለከቱትና የአበበ ቢቂላ ተወዳዳሪዎቹን በርቀት ጥሎ ማሸነፉ ትንግርት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የትናየት አባቱ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ሲወዳደር ያደረጋቸውን ልዩ ልዩ ትጥቆች ይዞ በመቅረብ አሳይቷቸዋል፡፡ አበበ በቶኪዮ ሲያሸንፍ የተነሳውን ፎቶግራፍም በስጦታ ማበርከቱ ይታወሳል፡፡

• ታሪክና አፈታሪክ በገድለ አበበ ቢቂላ

ነገር በነገር ቢወሳ አይደንቅምና በኩሩ (ዘ ሌጀንድሪ) አበበ ቢቂላ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከግማሽ ምእት ዓመት በፊት ያስመዘገባቸው ተደጋጋሚ ድሎቹና ስኬቶቹ ለአፈታሪክነትም የበቁበት አንዳንድ አጋጣሚዎችን እዚህ ላይ ማንሳት ይገባል፡፡

አበበ የአትሌቶች በኩር በመሆኑ፣ የመጀመሪያ ውድድሩንም በባዶ እግሩ በመሮጥ የተፈጸመ በመሆኑ ክንውኑን ከታሪካዊ እውነታ ባሻገር አፈታሪክ ውስጥም እንዲገባ አስችሎታል፡፡ ኅብረተሰቡ የራሱን አፈታሪክ ፈጥሮለታል፡፡ ጀግንነቱን ለማጉላትና ለማወደስ ከተፈጠሩት አፈታሪኮች መካከል በባዶ እግሩ የመሮጡ ምክንያትና ሮም ከነበረው የአክሱም ሐውልት ጋር የተያያዙ ተረኮች ይገኙበታል፡፡

አበበ ‹‹እኔ በባዶ እግሬ የምሮጥበት ምክንያት ጫማ አጥቼ ሳይሆን ኢትዮጵያ አገሬ ከጥንት ጀምሮ የጀግንነት ሙያ በድፍረትና በቆራጥነት የምትፈጽም መሆኑን ለዓለም በይፋ ለማሳወቅ ነው፤›› ማለቱ በዘመኑ የተወሳ ነው፡፡

ሰዉ ደግሞ በአፈታሪኩ ለየት ያለ የራሱን ተረክ እየተቀባበለ አወጋው፣ ተረከው፡፡ እንዲህም አለ፡- ‹‹አበበ ቢቂላ በሮም የማራቶን ሩጫውን ሲጀምር ጫማ ተጫምቶ ነው፡፡ ሩጫውን እያጋመሰ ሳለ ‹እንዴ የአገሬን ዳገት ቁልቁለቱን የወጣሁት የወረድሁት በባዶ እግሬ አይደለም እንዴ፣ ሶላቶ ጣሊያን ባለበት አገር ጫማዬን አውልቄ ነው የምሮጠው ብሎ አሽቀንጥሮ ጥሎ በመሮጥ ድሉን ፈጸመ፤›› አሁንም በተለይ ወግና ተረቱ ላይ በሚያተኩሩት ዘንድ መወሳቱ አልቀረም፡፡

አበበ ቢቂላና አበበ ዋቅጅራ (እርሱም በባዶ እግሩ ነበር የሮጠው) ከአሠልጣኞቻቸው ስዊድናዊው ኦኒ ኒስካነን ጋር ከውድድሩ ቀናት በፊት የመወዳደሪያ ሥፍራውን መመልከታቸው አበበም ከአቅራቢያው የሚገኘውን ታሪካዊውን የአክሱም ሐውልትን ማስተዋሉ እውነት ነው፡፡

‹‹አበበም አክሱም ሐውልቱን ተመልክቶ ወኔው ተቀሰቀሰ፡፡ የዘመኑን ታላቅነትና ኃያልነት አስተዋለ፡፡ ከኢትዮጵያ ተዘርፎ ሮም መቆሙ ቆጭቶታል፤ አስከፍቶታል፡፡ ግን እንደ አክሱም የዓለም ገናና ታሪክ እርሱም መግነን፣ መንገሥ ሽቷል፡፡ እጅ ላለመስጠት፣ ላለመረታት ቃል ገባ፤›› አፈታሪክ ነው፡፡

አበበ ቢቂላ ጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም. በሮም ኦሊምፒክ ድሉን ዘከረ፡፡ ባለ 11 ቁጥር መለያው ሹራቡን ለብሶ ከነፈ፡፡ የመጀመርያው ጥቁር አፍሪካዊ የማራቶን ባለወርቅ ሆነ፡፡

‹‹በባዶ እግሩ! በእውነት እናስብ! ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ መሮጥ ጨርሶ ያልተለመደ፣ ከእነሱ በፊትም ሆነ ኋላ ተደርጎም ተተርኮም የማይታወቅ›› እንዳለው የኦሊምፒክ ሪቪው አዘጋጅ፡፡ ከሮም አራት ዓመት በኋላ ቶኪዮ ማራቶንና አበበ ዳግም በድል ተገናኙ፡፡

• መታሰቢያዎቹ

የአበበ ቢቂላ አንፀባራቂ ድሎች ለአፍሪካውያን በፋና ወጊነት ጠቅሟቸዋል፡፡ በኩራችን ብለውም ሰይመውታል፡፡ አዲስ አበባ በ2000 ዓ.ም. ያዘጋጀችውን 16ኛውን የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አጋጣሚን ምክንያት በማድረግ በ50 ዓመታት ውስጥ ለአፍሪካ አኩሪ ታሪክ የፈጸሙ አትሌቶች ሲሸለሙ፤ አውራው ተሸላሚ አበበ ቢቂላ ነበር፡፡ ‹‹የአፍሪካ ማራቶን አባት›› ተብሎም በዶክመንተሪው ፊልም ላይ ተመልክቷል፡፡ ታላቁን ሽልማትም ልጁ የትናየት አበበ ቢቂላ ከነፍስ ኄር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እጅ መቀበሉ ይታወሳል፡፡

አፍሪካውያን ለአበበ ያላቸው ፍቅርና አክብሮት እስከ አይባልም፡፡ የአፍሪካ አትሌክስ ሻምፒዮና በሴኔጋል መዲና በዳካር በ1971 ዓ.ም. ሲጀመር ወደ ዳካር ስታዲየም የሚያስገባውን መንገድ ‹‹አበበ ቢቂላ ጎዳና›› በማለት የሴዳር ሴንጎር አገሯ ሴኔጋል መሰየሟ ይታወሳል፡፡

ኢጣልያም ለአበበ ክብሩን አልነፈገችም፡፡ የሮም ኦሊምፒክ 50ኛ ዓመትን ስትዘክር አንድ ድልድይ በስሙ ሰይማለች፡፡ ኢትዮጵያስ? አዲስ አበባና አዳማ ስታዲየሞቻቸውን በአበበ ቢቂላ መሰየማቸው ይጠቀሳል፡፡

ከ16 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘውን ፒኮክ መናፈሻ ወደ ኢትዮ ጃፓን መናፈሻ በመለወጥ ለአበበ ቢቂላ የመታሰቢያ ሐውልት እንደሚቆምለት ተነግሮ የነበረው ሁኔታ ከምን ደርሶ ይሆን? በቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ስፖርትና ኦሊምፒክ መሪዎች ዘመን ለአበበ ቢቂላ መዘከሪያ፣ ለድሎቹ መታወሻ ይሆን ዘንድ በአዲስ አበባ ስታዲየም ምዕራባዊ በር 11 ቁጥር መግቢያ አጠገብ የተተከሉት ምስሎቹስ የት ደረሱ?

• የተዛባው ታሪክ

ነገር በነገር ቢወሳ አይደንቅምና ታላቁ አበበ ቢቂላም ሆነ ሌሎቹ አትሌቶቻችን በኦሊምፒክም ሆነ በዓለምና በአህጉር አቀፍ ደረጃ ያስመዘገቧቸውን አንፀባራቂ ድሎች ባግባቡ ሳይዛነፍና ሳይዛባ በታሪክ ሰነድነት ለማቆየት በሚደረገው ጥረት ላይ ክፍተት  እንዳለ ማስረጃ መደርደር ይቻላል፡፡ የባሕር ማዶ ጋዜጠኞችንና ተንታኞችን ያህል፣ አትሌቶቻችን ያቀዳጁንን ክብር ያህል፣ ድላቸውንና ታሪካቸውን አለመመዝገብ ያሳስባል፡፡ ለማሳያ ያህል ሌላውን ትተን የዓመት ቁጥርን ብቻ ብንመለከት ቀደም ሲል የታተሙ አንዳንድ መጽሔቶች የአበበ ቢቂላን የ1957 ዓ.ም. የቶኪዮ ድል በ1956፣ የማሞ ወልዴን የ1961 ዓ.ም. የሜክሲኮ ድል በ1960፣ የ1993 ዓ.ም. የነኃይሌ ገብረሥላሴን ድል በ1992 እንደሆነ እያደረጉ በመጻፍ እነሱ ተሳስተው ሌሎችን ሲያሳስቱ ኖረዋል፡፡

ለአገር ቤትና ለውጭ አገር የመረጃ ምንጭ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ‹‹ኢንሳይክሎፒድያ ኢትዮፒካ›› ቅጽ1 ከ10 ዓመት በፊት በጀርመን እውን ሲሆን፣ ስለ አበበ ቢቂላ የተጻፈው በአሳዛኝ መልኩ ፈጽሞ የተዛባ ነው፡፡ የልደትና የዕረፍት ዘመኑን፣ የትውልድ ቦታው የሚገኝበት ክፍለ ሀገርና በቶኪዮ ያስመዘገበው ጊዜ ሁሉም የተሳሳተ ነው፡፡ ኢንሳይክሎፔዲያው ‹‹አበበ ቢቂላ ኖቬምበር 20 ቀን 1927 [ኅዳር 11  ቀን 1920 ዓ.ም] በደቡብ ሸዋ፣ ደብረብርሃን አውራጃ፣ ዋዩ ወረዳ ተወልዶ በ46 ዓመቱ ኦክቶበር 27 ቀን 1973 [ጥቅምት 17 ቀን 1966 ዓ.ም.] አረፈ፡፡ በሮም ኦሊምፒክ (1960) በ2 ሰዓት 15 ደቂቃ 15.2 ሰከንድ፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ (1964) በ2 ሰዓት 12 ደቂቃ 12.2 ሰከንድ የሆነ ጊዜ በማስመዝገብ አሸነፈ›› ይላል (የተሰመሩት በሙሉ ስህተቶች ናቸው)፡፡

እውነታው ግን አብዱ አሕመድ በ1967 ዓ.ም. ባሳተመው የአበበ ቢቂላና የማሞ ወልዴ ታሪክ መጽሐፍ ላይ እንደተቀመጠው (በሌሎች የአገር ቤትና የውጭ መጻሕፍት ጭምር እንደተመለከተው) አበበ በቀድሞ አጠራር በሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ (በአሁን አጠራር ሰሜን ሸዋ) በደብረብርሃን አውራጃ፣ ደነባ፣ ልዩ ስሙ ጃቶ ከሚባለው ቀበሌ ነሐሴ 30 ቀን 1925 ዓ.ም. መወለዱን ጥቅምት 15 ቀን 1966 ዓ.ም. ሐሙሱ ጧት ልክ ለሦስት ሩብ ጉዳይ ላይ በ41 ዓመቱ ማረፉ ተመዝግቧል፡፡ የማራቶኑ ጀግና አበበ ቢቂላ በሮም ኦሊምፒክ ክብረወሰኑን በመስበር ያስመዘገበው ትክክለኛ ጊዜ 2 ሰዓት 15 ደቂቃ 16.2 ሰከንድ ነው፡፡ በቶኪዮ ኦሊምፒክም የዓለም ክብረወሰንና በርሱ የተያዘውን የኦሊምፒክ ክብረወሰን የሰበረበት ትክክለኛ ጊዜ በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሰነዶች የተረጋገጠው 2 ሰዓት 12 ደቂቃ 11.2 ሰከንድ ነው፡፡

ሌላው የተዛባ ታሪክ መዝግቦ ለዓለም ያሠራጨው ጉግል ድረ ገጽ ነው፡፡ ሐቻምና በነሐሴ ወር በአንዱ ዕለት ‹‹ታሪክ›› ብሎ በመፈለጊያ ገጹ ላይ አበበ ቢቂላ ‹‹ኦገስት 7 ቀን 1932›› ተወለደ ብሎ በሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ በአሸናፊነት የመጨረሻ መስመሩን በጥሶ ሲያልፍ ያሳያል፡፡

ጉግል በነሐሴ መባቻ ዝክሩ ከየት እንዳገኘው የማይታወቅ እሱም መረጃዬ ይሄ ነው ብሎ ያልጠቀሰው የሚገርምና የሚያሳዝን ‹‹ታሪክ›› አስፍሯል፡፡ ‹‹አደበ ቢቂላ›› (ስሙን በትክክል አበበ ብሎ እንኳን አላሰፈረውም) ከመነሻው ከ1960ው (1952 ዓ.ም.) የሮም ኦሊምፒክ ቡድን ውስጥ አልተካተተም ነበር፤ ዋሚ ቢራቱ ‹‹እግር ኳስ ሲጫወት›› በመጎዳቱ ምክንያት ‹‹እርሱን ተክቶ እንዲያውም አውሮፕላኑ ከመነሣቱ በፊት ነው የተጓዘው›› የሚል ተረት ተረት አስፍሯል፡፡ አበበ በአዲስ አበባ ማራቶንን 2 ሰዓት ከ25 ደቂቃ በመግባት የተደነቀና በወቅቱ ቁጥር አንድ ተመራጭ እንደነበረ ታሪክ በአግባቡ መዝግቦታል፡፡ የተዘባረቀው የጉግል መረጃ ምንጩ፣ ፖል ራምባሊ የጻፈው ‹‹Barefoot Runner The Life of A Marathon Champion›› ልቦለድ ተኮር መጽሐፍ ይሆን? ይህን መጽሐፍ ሐቻምና ትኩዕ ባሕታ ‹‹ሮማን የወረረ ጀግና ያልተዳሰሰው የሕይወት ጉዞ›› ብሎ ተርጉሞ ማሳተሙ ይታወሳል፡፡

• ሲጠቃለል

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ክብር ዘበኛ ሠራዊት ሻምበል የነበረው አበበ ቢቂላ፣ ከአፈታሪክ ሌላ በሕዝባዊ ዘፈንም ሲነሳ ኖሯል፡፡ አንዱ ከበኩር ድምፃዊው የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ጋር የተዛመደበት ነው፡፡

‹‹ያገባሻል ያገባሻል

አበበ ቢቂላ ያገባሻል

ይድርሻል ይድርሻል

ጥላሁን ገሠሠ ይድርሻል››

በ1960ዎቹ ሲዘፈን የነበረው

‹‹ማራቶን ማራቶን

ማራቶን ልዕልቷ

አበበና ማሞ ሆኑ ባለቤቷ››

ኢትዮጵያ ለሦስተኛ ጊዜ በሜክሲኮ ኦሊምፒክ (1961 ዓ.ም. መስከረም) በማሞ ወልዴ ድል አድራጊነት ስትቀዳጅ የተዜመ ነበር፡፡

ገድለ አበበ ቢቂላ ታሪካዊ የቁጥር እና የቀን መገጣጠሞችንም አቅፏል፡፡

አበበ በሮም ኦሊምፒክ (ጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም.) ያጠለቀውን 11 ቁጥር መለያ በቶኪዮ ኦሊምፒክ (ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም.) በ17 ቁጥር ቢለውጠውም፤ የሮጠበት ቀን 11ኛ (ጥቅምት) ነበር፡፡ የትርፍ አንጀት ቀዶ ሕክምናውን ረቡዕ (መስከረም 6 ቀን 1957 ዓ.ም.) ሲያደርግ፣ የቶኪዮ ድሉን ያጣጣመው ረቡዕ (ጥቅምት 11) ነበር፡፡

ከ50 ዓመታት በፊት አበበ ቢቂላ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ተፎካካሪዎቹን ጣጥሎ ለድል እየገሰገሰ የተመለከተች አንዲት ጃፓናዊት ‹‹አይ ላቭ ዩ›› ስትለው፣ ‹‹የላቡን ነገር ተይው›› ማለቱ አፈታሪኩ ያወሳል፡፡

Source
-http://www.ethiopianreporter.com/
-by:  ሔኖክ ያሬድ

Original Link
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/life-and-art/item/7618-%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%89%A0%E1%89%A0-%E1%89%A2%E1%89%82%E1%88%8B-%E1%8B%A8%E1%89%B6%E1%8A%AA%E1%8B%AE-%E1%8B%B5%E1%88%8D-%E1%8B%88%E1%88%AD%E1%89%83%E1%8B%8A-%E1%8A%A2%E1%8B%AE%E1%89%A4%E1%88%8D%E1%8B%A9