Questions about Love Sex
Questions about Love Sex

ያልተመለሱ ወሲብ ነክ ጥያቄዎቻችሁ እና አዳዲስ የሕክምናው ሳይንስ ምላሾች

በሴቶች በኩል የሚደፈር ርዕሰ ጉዳይ አይሁን እንጂ በርካታ ወንዶች በጋራ ሲሰበሰቡም ሆነ አንድ ለአንድ ሲያወሩ ወሲብ ነክ ጉዳዮችን አንዴ ወይም ሌላ ጊዜ ማንሳታቸው አይቀርም፡፡ በሴቶቹ ክብ ውስጥ ተገኝቼ ውይይታቸውን ባላዳምጥም እነርሱም ቢሆኑ ከጓደኞቻቸው ጋር ይህን ስሱ ርዕስ ሲያነሱና ሲጥሉ እንደሚቆዩ እገምታለሁ፡፡ በኛ አገር በወሲብ ነክ ጤና ጉዳዮች ላይ የህክምናው ሳይንስ ሰዎችም ይሁኑ ሚዲያው በግልፅ የመነጋገር እና ችግሮችን የማቅለል ልምዱ አነስተኛ በመሆኑ ወደ ጤና ተቋማት ለመሄድ እና የባለሞያን ሀሳብ ለማግኘት ተነሳሽነቱ ባይኖር ብዙ አይገርምም፡፡ ‹‹ቄሱም ዝም፣ መፅሐፉም ዝም›› በሆነበት የወሲብ ጤና ጉዳይ በውጪው ዓለም ለቁጥር የሚያታክቱ አማካሪ ባለሞያዎችና የፃፏቸው መፅሐፍት ለሰዎች የእለት ተዕለት ጭንቀቶች መፍትሄን ቢሰጡም እኛ አገር ገና ብዙ የሚቀረን እርምጃ አለ፡፡ ይህንን መነሻ አድርገን የተለያዩ ሴክስ ኤክስፐርቶች የፃፏቸውን መፅሐፍትና መጣጥፎች በማጣቀሻነት በመጠቀም በተለያየ ጊዜ የሚገጥመው ወሲብ ነክ ችግሮች እና ያልተመለሱ ጥያቄዎችን በመመለስ ግንዛቤን የሚያሲዝ አጭር ምልከታ ልናደርግ ወደናል፡፡

ምን ያህል ወሲብ? በየስንት ጊዜው?
በዚህ ለኑሮ መሮጥ የሁሉም ሰው ዕለታዊ የቤት ስራ በሆነበት ጊዜ በፍቅርም ይሁን ትዳር ውስጥ ያሉ ጥንዶች እርስ በእርሳቸው ፍቅራቸውን ለመግለፅ እና ወሲብ ለመፈፀም በቂ ጊዜ ላያገኙ ይችላሉ፡፡ ወሲብ መፈፀም አካላዊ ግንኙነት ብቻ ባለመሆኑ ሁለቱም ተጣማጆች አእምሮአቸው አሪፍ እና ዘና ብሎ ቅርርቡንም ፈልጎ ወደ ወሲብ ሲያመራ በእርካታ የሚያጥለቀልቅ እና አዝናኝ ጥምረትን ይፈጥራሉ፡፡ አንዳንድ ጥንዶች ግንኙነት ከፈፀሙ ረጅም ጊዜ ሆኗቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ሌሎች ጥንዶች በሳምንት አሊያም በወር ምን ያህል ጊዜ ይሆን ወሲብ የሚፈፅሙት? ሲሉ በውስጣቸውም ይጠይቃሉ፡፡ በሳምንት፣ በወር ይህን ያህል ጊዜ ወሲብ ሊፈፅም ይገባል የሚል ምትሃታዊ ቁጥር የለም፡፡ የህክምና ሳይንስ ባለሞያዎችም ቁርጥ ያለ መልስ አይሰጡም፡፡ ‹‹ይህ በግንኙነቱ ጤናማነት ደረጃ እና በጥንዶች ቅርርቦሽ የሚወሰን ነው›› ባይ ናቸው፡፡
ሆኖም ግን ጤናማ ግንኙነት ውስጥ ያሉ ጥንዶች ወሳኝ ጉዳዮች መካከል ፍቅር መስራት ዋነኛው እንደመሆኑ በግንኙነት ቆይተው ለበርካታ ወራት ወሲብ ካልፈፀሙ ጥያቄ ማንሳቱ ጤናማ ነው፡፡ ለምን ያህል ድግግሞሽ እና መቼ የሚለውን ለማጥናት ሙከራ ያደረጉ ተመራማሪዎች ያሳተሙት ውጤት መነሻ ሀሳብን ሊሰጥ ይችላል፡፡ ዱሬክስ ኩባንያ 2006 ላይ ያወጣው ዓለም አቀፍ ሴክስ ሰርቬይ ላይ ዝቅተኛ ወሲብ ይፈፅማሉ የተባሉት የሲንጋፖር ሰዎች ሲሆኑ በወር 6 ጊዜ ነው ወሲብ የሚፈፅሙት፡፡ ባለሞያዎች በመጨረሻ የሚያጠቃልሉት ወሲብ የሚፈፀምበት ድግግሞሽ በሁለቱ ጥንዶች ስምምነት ያለው ከሆነ በፍቅር ግንኙነቱ አለዚያም ትዳሩ ላይ የሚፈጠር ችግር የለም፡፡ ይሁንና ከሁለቱ አንዱ ወሲብ እየፈለጉ ሌላኛው ወገን የሚያዘገየው ከሆነ በጉዳዩ ላይ በግልፅ ተወያይተው ሁለቱንም የሚያስማማ የጊዜ ርቀት እንዲያስቀምጡ እና ስሜታቸውን ተረድተው ቢዝናኑበት መልካም ነው ይላሉ፡፡

በወሲብ ስንት ደቂቃ ይቆያሉ? ቀድሞ የመጨረስ ጣጣ
በርካታ ወንዶች ወሲብ እየፈፀሙ በርካታ ደቂቃዎችን መቆየትን በፍቅር እና ትዳር አጋራቸው ዘንድ ነጥብ ያስቆጥርልናል ብለው ያስባሉ፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን በዚህ መነሻነት በሚፈጠር መጨናነቅና የስነ ልቦና ውጥረት ገና እንደደረሱ ጨርሰው ለማቆም የሚገደዱት ናቸው የሚበረክቱት፡፡
በወሲብ የመቆየት ጊዜ ምን ያህል መሆን አለበት ለሚለው የተለያዩ የህክምና ሳይንቲስቶችና መፃህፍት የተለያዩ ምላሾችን ይሰጣሉ፡፡ በህክምናው ቋንቋ Intravaginal Ejaculatiry Latency Time (IELT) የሚባለው የቆይታ ጊዜ የሚቆጠረው ወንዱ በሴቷ ብልት ውስጥ ብልቱን ከከተተበት ደቂቃ ረጭቶ እስከሚወጣበት ድረስ ያለው ነው፡፡ ‹‹ይህ ጊዜ ልክ አንድ ደቂቃም ይሁን አንድ ሰዓት ወሳኝ ሊሆን የሚገባው በዚህ ጊዜ ሁለቱም ተጣማጆች እኩል እርካታን ከወሲብ ተጎናፅፈዋል ወይ የሚለው ነው›› ይላሉ ዶ/ር ሄለን ኦኮኔል የተባሉት የኒውሮሎጂ ባለሞያና የወሲብ ጉዳዮች አማካሪ፡፡ በደቂቃ ልኬን ማወቅ አለብኝ ለሚሉ ወንዶች መልስ ቢሆን ብለው በአማካይ አንድ ወንድ በወሲብ መቆየት ያለበትን የደቂቃ ርዝመት ያጠኑ ባለሞያዎች እ.ኤ.አ 2005 ላይ ጆርናል ኦፍ ሴክሹዋል ሜዲስን በተሰኘ የምርምር መፅሔት እንደፃፉት በአማካይ አንድ ወንድ ወሲብ እያደረገ ሊቆይ የሚችለው ለአምስት ደቂቃ ከ30 ሰከንድ ያህል ነው፡፡ ይህ ቆይታ ታዲያ ቅድመ ዝግጅቱን መተሻሸቱን እና መሳሳሙን አይጨምርም፡፡ ብልቱ ከሴቷ ብልት ገብቶ ስፐርሙን እስካፈሰሰበት ቅፅበት ያለውን ብቻ ይመለከታል፡፡ የጥናቱ አድራጊዎች ገና እንደገቡ የሚያፈሱ ሰዎችን አስመልክተው ሲፅፉ ‹‹ወሲብ መዝናኛ ነው፣ ዘና ብለው ከሴቷ ብልት መቆየታቸውን እንደ ደስታ እያሰቡ ሳይጣደፉ የሴቷ ደግሞ ስሜት እያደመጣ ወሲብ ማድረግን ይልመዱ›› ሲሉ መክረዋል፡፡ ከፍርሃት፣ ከጭንቀት እና መጠራጠር የፀዳ ንፁህ ግንኙነት ውስጥ ያሉ ጥንዶች የሚቆዩበትን ጊዜ እንዳሻቸው ሊለጥጡት ይችላሉ፡፡ ‹‹ወሳኙ የስነ ልቦናዊ ጥምረታቸው ልክ ነው›› ይላሉ የጥናቱ መሪ አያን ኬርነር፡፡ አካላዊ እና ከብልት ጡንቻዎች ጋር የተያያዘ ችግር ካለ ይህን በህክምና ማስታገስ እንደሚቻልም ያክላሉ፡፡

በወር አበባ ጊዜ ሴክስ ይፈቀዳል?
ሴቶች የወር አበባ ላይ በሚሆኑበት ወቅት አንዳንድ ጊዜ ተጣማጆቻቸውን ሴክስ ይከለክላሉ፡፡ ‹‹አሞኛል›› ይላሉ፡፡ እውን በወር አበባ ጊዜ ወሲብ መፈፀም ህመም ይሆናል? የጎንዮሽ ጉዳትስ ይኖረው ይሆን? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ወንዶችም ሴቶችም መልስ እንዲሆን ታዋቂዋ የሴክስ ኤክስፐርት እና የጉድቫይብስ መፅሔት ፀሐፊ ካሎል ኩዊን ያቀረቡት ፅሑፍ የሚለውን እንመልከት፡፡ ኤክስፐርቷ እንደሚሉት በወር አበባ ጊዜ ወሲብ መፈፀም ችግር የለውም፡፡ ይሁንና በአንዳንድ ሀይማኖታዊ ምክንያቶች የተነሳ ብዙ ሴቶች ከወሲብ ሲታቀቡ እንዳስተዋሉ ተናግረዋል፡፡ በሳይንሱ ግን አይከለከልም፡፡ እንዲያውም በወር አበባ ወቅት ከሚከሰተው ህመም የሚገላግልና የመዝናናት ስሜትን የሚፈጥሩት ኢንደርፊን የተባሉት ሆርሞኖች ሴክስ በሚፈፅሙ ወቅት በሰውነታቸው ስለሚለቀቅ ራስ ምታት፣ ድብርት እና ቀርጠት የመሳሰሉት የወር አበባ ህመሞችን ማስታገስ እንደሚችሉ ባለሞያዋ ያብራራሉ፡፡ ይሁንና የወር አበባ ወቅት የማህፀን ጫፍ ደሙን ለማስወጣት ከፈት የሚልበት በመሆኑ እንዲሁም የብልታቸው አካባቢ ከወትሮው በተለየ አሲዳማነቱ የሚቀንስ በመሆኑ ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች እና አባላዘር በሽታዎች የሚጋለጡበትም ወቅት ስለሚሆን ሁልጊዜም ኮንዶም መጠቀምን አይርሱ ሲሉ ሀሳባቸውን ያጠቃልላሉ፡፡

ወሲብ በጠዋት የጤና ነው?
የባለቤቷ የወሲብ ፍላጎት ጉዳይ ያሳሰባት ሴት ባቀረበችው ጥያቄ እርሱ ወደ ቤት ማታ ሲመጣ ደካክሞ ይመጣና ይተኛል፡፡ ጠዋት ላይ ግን አፈፍ ያደርገኝና ወሲብ መፈፀም እንጀምራለን፡፡ ይሄ የሌሎች ወንዶች ተፈጥሮ ይሆን ወይ? የጤናስ ነው? ስትል ትጠይቃለች፡፡ ለእርሷና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄ ለሚኖራቸው ሰዎች ኤክስፐርቶቹ የሚሉት አላቸው፡፡ በእርግጥም የወንዶች ተፈጥሯዊ የሆርሞን ስርዓት የሚፈጥረው ፍላጎት አለ፡፡ የወንዶች የወንዴ ሆርሞን ቴስቴስትሮን መጠን በቀን ውስጥ ከፍ እና ዝቅታ ይገጥመዋል፡፡ በተለይ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት መጠኑ ከፍ ብሎ የሚገኝበት በመሆኑ ወሲብ ቢጠይቅ አትፍረጂበት ይላሉ ዩሮሎጂስት ሐኪሟ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ያደረ ሽንት በሽንት ከረጢት ስለሚጠራቀም ግፊቱ ደም ወደ ብልቱ በብዛት እንዲደርስና ብልቱ እንዲወጠር ያደርጋል፡፡ እነዚህ የሆርሞኖችና በደም ፍሰቱ የብልት መወጠር ምክንያቶች በጠዋት ለወሲብ መነቃቃቱ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የጠዋት ጉልበትና ብርታቱም ሳይነዘጋ፡፡

የ‹‹ጂስፖት›› አገር ከወዴት ነው?
ሴቶችን የማርካት ፈተና
ሴቶች በወሲብ መርካታቸው ጉዳይ እንደ ሁለተኛ ነገር ሲወሰድ የነበረበት ዘመን አብቅቶ ዛሬ ዛሬ አብዛኛዋ ሴት ከፍቅር እና ትዳር ግንኙነቷ ከወንድ እኩል የወሲብ እርካታን ትፈልጋለች፡፡ የሴክስ ኤክስፐርቶች ይህን የእርሷን እርካታ ለማረጋገጥ የሚሻ ወንድ ሰውነቷን፣ ስሜቷ የሚቀሰቀስበትና ከእርካታም የሚያደርሷትን ቦታዎች ልቅም አድርጎ ማወቅ ይገባዋል ይላሉ፡፡ ሴቷን ብልት ቁልፍ የእርካታ ስፍራ ‹‹ጂስፖት› ማወቅ የሁሉም ወንድ የቤት ስራ መሆን አለበትም ይላሉ፡፡ ትክክለኛ ቦታውን በመጠቆም በኩል እንዲሁም ከነጭራሹ ስለመኖሩ የሚጠራጠሩ ባለሞያዎች ቢኖሩም በአመዛኙ ግን ጂ ስፖት ቁልፍ የሴቷ የእርካታ ማዕከል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህ ስፍራ ጥንት በህንድና ቻይና ፅሑፎች በግምት ሲገለፅ የኖረ ቢሆንም በዘመናዊ የህክምና ሳይንስ የታወቀው በጀርመናዊው የማህፀን ስፔሻሊስት ዶ/ር ኸርነስት ግራፊንበርግ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በእርሱ በመታወቁም ይህ የሴቶች የእርካታ ማዕከል በአባቱ ስም የእንግሊዝኛ ፊደል ‹ጂ› በመውሰድ ‹ጂ ስፖት› ተባለ፡፡ እርሱ እንደሚገልፀው ጂስፖት የሚገኘው በሴት ብልት ፊት ግድግዳ በብልቷ የላይኛው ጫፍ እና በብልቷ ስንጥቅ መካከል ነው፡፡ ይህ ስፍራ በጣትም ሆነ በወንድ ብልት በሚነካካበት ወቅት በሚፈጠር የነርቮች መነቃቃት ወደ እርካታ ጫፍ ትስፈነጠራለች፡፡ የወንዱ ብልት ሲገባና ሲወጣም ይህን ስፍራ እንዲነካካ ካልሆነለትም በጣቱ ጭምር እንዲያነቃቃው የሴክስ ኤክስፐርቶቹ ይመክራሉ፡፡

ወሲብ በብርሃን ወይስ በጨለማ?
በርካቶች ወሲብ ሲፈፅሙ መብራት ያጠፋሉ፡፡ ከፊሎች ደግሞ መብራት በርቶ እርስ በእርስ እየተያዩ ሁለ ነገራቸውን እያደነቁ መፈፀሙ የተሻለ እርካታ ይሰጣቸዋል፡፡ በወሲብ ጉዳዮች የሜንስ ሄልዝ መፅሔትን የሚያማክሩት ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት እንደሚሉት በብርሃን ወይም በመብራት ወሲብ መፈፀም ዝግጁ የሆኑ ጥንዶች በግንኙነታቸው ጥልቀትና ግልፅነት የሚተማመኑ፣ ተጣማጃቸውን የሚያፈቅሩ፣ የወሲብ አካላቶቻቸውን ብቻ ሳይሆን መላ አካላትና መንፈሳቸውም ጥምረት እንዲፈጠር የሚፈልጉና የሚፈቅዱ በመሆናቸው ሊደሰቱ ይገባል፡፡ ግን ደግሞ ጭለማው እና መብራቱ መጥፋቱም በመጥፎ ምልክትነት ሊወሰድ አይገባም፡፡ አንዳንድ ተፈጥሮ ይህን አይፈቅድም፡፡ ሁለታችሁ ብቻ ባላችሁበት ክፍል ሁልጊዜ መብራት እንዲጠፋ የምትፈልጉ ከሆነ ግን እስቲ አብርታችሁ ሞክሩት፡፡ ስለግንኙነታችሁ አንዳንድ ነገር ሊገልጥላችሁ ይችላል፤ ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን ከወሲብ ህይወት ጋር ተያይዘው ሊነሱ እንደሚገባቸውና ምላሽ እንደሚፈልጉ እንረዳለን፡፡ በሌላ ጊዜ ርዕሰ ጉዳዩን ልናነሳው ቀጠሮ ይዘን የዛሬን እናብቃ፣ ሰላም!

Source

Source

– Via : zehabesha.com

Original Link
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/32403