-ከ500,000 ብር በላይ ግምት የተከፈለባቸው ቤቶች በ20,000 ብር ይሸጣሉ ተብሏል

-ባለቤቱ ላፍርስ ሲል ዋጋው ከፍ ተደርጎ መገመቱ ይነገራል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመልሶ ማልማት ያፈረሳቸውና በሚያፈርሳቸው መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ቦታዎችና የተለያዩ ይዞታዎች ላይ  ነዋሪዎች ቅሬታ እያቀረቡ ነው፡፡

ነዋሪዎቹ የሚያቀርቡት ቅሬታ ይዞታ ‹‹ለምን ለልማት ፈረሰ?›› ሳይሆን፣ የራሳቸውንም ይዞታ ሆነ ከቀበሌ የተከራዩትን ቤት እንዲለቁ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ሲለቁ፣ ቤቱን በማፍረስ ሒደት ላይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በተለይ በአራዳ በቂርቆስ፣ በቦሌና በየካ ክፍላተ ከተሞች የሚኖሩ ባለይዞታዎች ይዞታቸውን በመልሶ ማልማት ምክንያት እንዲለቁ ሲደረጉ፣ የኖሩበትን ቤት ራሳቸው አፍርሰው የግንባታ ዕቃዎችን ለመውሰድ የሚመለከተውን የከተማ አስተዳደር ሲጠይቁ  ፈቃደኛ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ተፈናቃዮቹ በብዙ ውጣ ውረድ እንዲያፈርሱ ከተፈቀደላቸው ግምቱን የሚያወጡት በየክፍላተ ከተማው በከተማ ማደስ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሚገኙ ገማቾች፣ ከሚፈርሱ ቤቶች የሚገኙ የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ እጅግ በጣም እንደሚያስወድዱ ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ቤቶች በጭቃ ከተሠሩ በኋላ በሲሚንቶ ስለሚገረፉ የግንባታ ዕቃዎችን መለየት እንደማይቻል የሚናገሩት ባለይዞታዎቹ፣ ገማቾቹ ግን የቤቱን ይዞታ ብቻ በማየት የተጋነነ ግምት በመስጠት ለኪሳራ እንደሚዳርጓቸውም ገልጸዋል፡፡

በመልሶ ማልማት የሚነሱና መልሶ ለማልማት አቅም ያላቸው ነዋሪዎች ወይም ነጋዴዎች ቅድሚያ የማልማት መብት ሊሰጣቸው ሲገባ፣ ‹‹ካፀዳን በኋላ በሊዝ ስለምንሸጥ የዚያን ጊዜ ከቻላችሁ መወዳደር ትችላላችሁ፤›› የሚል ምላሽ በመስጠት ተገቢ ያልሆነና አስተዳደሩ ራሱ ያወጣውን መመርያ ራሱ ማፍረሱ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

በየክፍላተ ከተሞቹ ያሉ የወረዳዎች ኃላፊዎች እስከ ማዕከል ድረስ ግንኙነት እንዳላቸውና ለመልሶ ማልማት የሚፈርሱ ቤቶችን፣ ባለቤቶቹ ተከራዮቹ እንዲያፈርሱ እንደማይፈልጉ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ የክፍላተ ከተማው የመልሶ ማልማትና ከተማ ማደስ መሐንዲሶች ለሚፈርሰው ቤት ዋጋ ካወጡ በኋላ ለወረዳ ኃላፊዎች እንደሚያስተላልፉ ጠቁመዋል፡፡ የወረዳዎቹ ሹሞች ቤቱ መፍረስ ያለበት በጥቃቅንና በአነስተኛ በተደራጁ ወጣቶች መሆኑን ይገልጹና በአካባቢው ሥራ ፈትተው የተቀመጡ ወጣቶችን በቡድን ተደራጅተው እንዲቀርቡ በድብቅ ተነግሯቸው እንደሚደራጁ ገልጸዋል፡፡

ሹሞቹ ለምሳሌ አንዱን ቤት በ20,000 ብር እንዲያፈርሱና እጅ በእጅ ክፍያ እንዲፈጽሙ በመነጋገር ሥራውን ከሰጧቸው በኋላ፣ ለይምሰል የተደራጁት ወጣቶች መርካቶ ምን አለሽ ተራ ለዚሁ ተግባር ከሠለጠኑና ከተደራጁ ነጋዴዎች ጋር በመነጋገር፣ ለወረዳው ሹሞች 20,000 ብር ከፍለው የሚፈርሰውን ቤት እንደሚረከቡ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

የወረዳው ሹሞች በወረዳው ከተማ ማደስ ግምት የተሸጠው ነባር ቤት እንደየቤቱ ይዞታ እስከ 500,000 ብር እንደሚጠራና ሁሉም ከላይ እስከታች የድርሻቸውን እንደሚያገኙም ነዋሪዎቹ ግምታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም ለረዥም ዓመታት የኖሩ ባለይዞታዎችና ተከራዮች የሚጠይቁት ታክስ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ወይም የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ‹‹ለምን ዝም አሉ?›› የሚል ነው፡፡ መንግሥት ከሽያጩ ገቢ እንደሚያገኝ ገማቾቹ የሚናገሩ ቢሆንም፣ ግምቱ እጅግ በጣም የወረደ በመሆኑ የታክስ ግኝቱም በጣም ትንሽ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች መመልከት ያለባቸው የመጨረሻ ገዥ የተባለው አካል ምን ያህል እንደሚሸጠው መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

ከነዋሪዎቹ ቅሬታና አቤቱታ በመነሳት የሚመለከታቸውን የወረዳ ጽሕፈት ቤቶች ለማነጋገር ሪፖርተር የሞከረ ቢሆንም፣ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ ወረዳ አላገኘም፡፡ ከአራዳ ክፍለ ከተማ ግን አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ኃላፊ እንደተናገሩት፣ በመልሶ ማልማት ስለሚነሱ ቤቶች ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት ግምት ሠርቶ ለወረዳው ጽሕፈት ቤቶች ያስተላልፋል፡፡ የወረዳው የሚመለከታው ኃላፊዎች በወጣው ዋጋ መሠረት ለአፍራሽ ግብረ ኃይል ይሰጣሉ፡፡ አፍራሽ ግብረ ኃይሉ የተገመተውን መጠን ከከፈለ በኋላ የሚያፈርሰውን ቤት ተረክቦ እንደሚያፈርስና ወረዳውም ከተቀበለው ግምት ላይ ለገቢዎች ክፍያ እንደሚፈጽም አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ሐሜቶች እንዳሉና መለስ ብሎ ማየት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

SOURCE
-Via:ethiopianreporter.com
-Writen by:ታምሩ ጽጌ
Original Link
http://www.ethiopianreporter.com

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.