State of Cybersecurity in Ethiopia
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ተከሰሰ

‹‹ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችን የሚያስረው በምርጫ 2007 ያለተቀናቃኝ ለማለፍ ነው›› ሰማያዊ ፓርቲ

‹‹የታሰሩት ከምርጫ ጋር በተገናኘ ሳይሆን በሽብር ስለተጠረጠሩ ነው›› መንግሥት

በምን እንደተጠረጠሩ ግልጽ ሳይደረግላቸው ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር ላይ የሚገኙት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሐዊ ፓርቲ (አንድነት)

ሥራ አስፈጻሚና ምክር ቤት አባላትን በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ባለማድረጉ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይልን መክሰሱን የመኢአድና አንድነት የውህደት አመቻች ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የመኢአድና የአንድነት ውህደት አመቻች ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የአንድነት ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የፓርቲው ምክር ቤት አባል አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣  የአረና የሕዝብ ግንኙንት ኃላፊ አቶ አብረሃ ደስታና የሰማያዊ ፓርቲ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ አቶ የሸዋስ አሰፋ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ሳይነገራቸው ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ከመንገድ ላይ ተይዘው ታስረዋል፡፡

በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19 (3) ላይ ተደንግጎ እንደሚገኘው፣ ዜጎች በተጠረጠሩበት ወንጀል ለመታሰር የሚያበቃ ምክንያት ስለመኖሩ፣ በፍርድ ቤት ምክንያቱ ተለይቶ እንዲገለጽላቸው የመጠየቅ መብታቸው በ48 ሰዓታት ውስጥ ሊከበርላቸው ቢገባም፣ ግብረ ኃይሉ ሕገ መንግሥቱን አክብሮ ሊያቀርባቸው አለመቻሉን ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራውና አቶ አበባው መሀሪ አስረድተዋል፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. የውህደት ስምምነት መፈረማቸውን ተከትሎ ውህደቱን ለማጠናቀቅ የውህደት አመቻች ኮሚቴ መቋቋሙንና ኮሚቴው የሚመራው በአቶ ሀብታሙ እንደነበር የገለጹት አመራሮቹ፣ ኢሕአዴግ የሁለቱን ፓርቲዎች ውህደት ባለመፈለጉ ሁኔታዎችን ለማደናቀፍ አባላቱን በቁጥጥር ሥር ሊያውል መቻሉን ገምተዋል፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች የጀመሩት ውህደት አባላቶቹን በማሰር ሊደናቀፍ እንደማይችል አመራሮቹ ገልጸው፣ ተጠርጣሪዎቹ ግን ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተከብሮ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ይገባ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የግብረ ኃይሉ ተግባር ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌውን የሚፃረር በመሆኑ፣ ታሳሪዎቹን ነፃ ለማውጣት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት ሐምሌ 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ክስ ማቅረባቸውን የገለጹት አመራሮቹ፣ ድርጊቱ ሕገ መንግሥቱን የጣሰ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ፍትሕ እንደሚሰጣቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ኢሕአዴግ ከአፍ ባለፈ መተግበር ያልቻለውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሳያነት ሊጠቀምበትና የቀጣዩን ዓመት ምርጫ በለመደው ሁኔታ ከቻለ አስሮና አደናግሮ፣ ካልተቻለም ጉልበቱን ተጠቅሞ ለመጠቅለል አባሎቻቸውን እያሰረ መሆኑን አመራሮቹ አስረድተዋል፡፡

የአንድነትና የመኢአድ ውህደት አመቻች ኮሚቴ አመራሮቹን በማሰቃየት፣ በማሸማቀቅ፣ በመደብደብና አካል በማጉደል የሚያደርገውን ተግባር በማውገዝ፣ አቶ ሀብታሙና አቶ ዳንኤል የታሰሩት በፖለቲካ አመለካከታቸውና በአቋማቸው ምክንያት  ብቻ በመሆኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ኢሕአዴግ በአሁኑ ወቅት ለውጥ ለማምጣት በቆራጥነት እየታገሉ ያሉ ሰላማዊ ታጋዮችን የሚያስረው፣ በአገር ውስጥ በሕጋዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ፓርቲዎችን ከአማፂ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸው በማስመሰል፣ ሰላማዊ ትግሉን ለማዳከም መሆኑን የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ መጪውን የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ያለተቀናቃኝ ለማለፍ የሚያደርገው ሕገወጥ እንቅስቃሴ እንደሆነም መገንዘባቸውን አመራሮቹ ገልጸዋል፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት እንዳስረዱት፣ የብሔራዊ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ የሸዋስ አሰፋ በሰላማዊ ትግሉ ውስጥ በቁርጠኝነት እየተሳተፉ ባለበት ሁኔታ ለእስር መዳረጉን አውግዘዋል፡፡ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ እንዲሁም አቶ አብረሃ ደስታ ለእስር መዳረጋቸው፣ ኢሕአዴግ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን አመላካች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢሕአዴግ ለራሱ የሚበጀውን እንዲከተል እንደሚያሳስቡና የፓርቲዎቹ አመራሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡

የፓርቲዎቹ አመራሮች ኢሕአዴግ አባሎቻቸውን እያሳደደ የሚያስረው መጪው 2007 አገራዊ ምርጫን በመፍራት መሆኑን አስመልክቶ የሰጡትን መግለጫ በሚመለከት፣ መንግሥት ያለውን ምላሽ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳን ሪፖርተር አነጋግሯቸው አጭር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ጌታቸው እንደሚሉት፣ ግለሰቦቹ የታሰሩት ሕጋዊ ፓርቲ ይዘው በሰላማዊ መንገድ ስለተንቀሳቀሱ ሳይሆን፣ ከሽብርተኞች ጋር ባላቸው ግንኙነት ተጠርጥረው ነው፡፡ ከምርጫም ጋር ሆነ ከሕጋዊ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ መንግሥት ማንንም እንዳላሰረና እንደማያስር ጠቁመው፣ በእስር ላይ የሚገኙት ግለሰቦች ግን በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት በሽብርተኝነት የፈረጀው የግንቦት 7 ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከየመን በቁጥጥር ሥር ውለው ወደ ኢትዮጵያ መተላለፋቸውን ተከትሎ ባስነገረው ዜና፣ በሕጋዊ ፓርቲ ውስጥ ተሰባስበው የሽብር ወንጀል ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ጋዜጠኝነትን ተገን በማድረግ ተመሳሳይ ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፣ ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. መግለጹ ይታወሳል፡፡

SOURCE
-Via:ethiopianreporter.com
-By:ታምሩ ጽጌ እና ነአምን አሸናፊ
Original Link
http://www.ethiopianreporter.com