በስኳር እጥረት ለስላሳ ፋብሪካዎች ሥራ እያቆሙ ነው
በስኳር እጥረት ለስላሳ ፋብሪካዎች ሥራ እያቆሙ ነው

በስኳር እጥረት ለስላሳ ፋብሪካዎች ሥራ እያቆሙ ነው

በአገሪቱ በተከሰተው የስኳር እጥረት ምክንያት የለስላሳ መጠጥ ኢንዱስትሪዎች ሥራ እያቆሙ መሆናቸውን አስታወቁ፡፡

ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ያገኙ የነበረው ስኳር በመቋረጡ ምክንያት ፋብሪካዎቹ የምርት ሒደታቸው እየተስተጓጎለ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፣ ኮርፖሬሽኑ መፍትሔ እንደሚኖር ገልጿል፡፡

በስኳር አቅርቦት ችግር የምርት ሥራቸው ከተስተጓጎለባቸው የለስላሳ መጠጦች አምራቾች መካከል አንዱ የሆነው ሞሐ የለስላሳ መጠጦች ድርጅት፣ ከሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ከኮርፖሬሽኑ ይሰጠው የነበረው ስኳር በመቋረጡ ምርት ማቆሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከኩባንያው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የስኳር አቅርቦት በመቋረጡ ምክንያት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የሚገኙ ሰባቱም ፋብሪካዎች ሥራ አቁመዋል፡፡ ሞሐ በቀን 75 ሺሕ ሳጥን ለስላሳ መጠጦች ለሽያጭ ያቀርብ የነበረ መሆኑን፣ የስኳር አቅርቦት በመቋረጡ ግን የኩባንያው ገቢ መጐዳቱን አስታውቋል፡፡

ኩባንያው በየዕለቱ ከሚሸጣቸው ለስላሳ መጠጦች መንግሥት ከተለያዩ ታክሶች ያገኝ የነበረውም 1.9 ሚሊዮን ብር የሚገመት ገቢ አሳጥቶታል ተብሏል፡፡

በስኳር እጥረት ሳቢያ የተፈጠረውን የምርት መስተጓጎል ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት እንዲያውቁት መደረጉን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ለፋብሪካዎቹ የሚሰጠው የስኳር ኮታ የተቋረጠበትን ምክንያት ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት በቴክኒክ ብልሽት የስኳር ምርት በመቀነሱ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር የኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽፈራው ጃርሶ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተፈጠረው ችግር ያጋጠመውን የስኳር እጥረት ለመሸፈን ሲባል ለለስላሳ ፋብሪካዎችና መሰል ድርጅቶች የሚሰጠው ስኳር ለጊዜው ተቋርጦ ለኅብረተሰቡ እንዲከፋፈል ተደርጓል ብለዋል፡፡

‹‹ሆኖም በቅርቡ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ምርት ስለሚጀምር ችግሩ እንደሚቀረፍ፣ ለተጠቃሚዎች መከፋፈል ያለበት ስኳር ግን እየተሰጠ ስለሆነ በሸማቾች ላይ ችግር አይኖርም፤›› ብለዋል፡፡ ስኳር ተጠቃሚ ፋብሪካዎችም በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ውስጥ እንደሚያገኙ አቶ ሽፈራው አረጋግጠዋል፡፡

ለምርታቸው በቋሚነት ስኳር ይቀርብላቸው የነበሩ ድርጅቶች በሥራቸው ላይ ተፅዕኖ በመፈጠሩ፣ ስኳር ከአገር ውስጥ የማያገኙ ከሆነ ከውጭ ለማስገባት መንግሥት ሌተር ኦፍ ክሬዲት እንዲያስከፍትላቸው አቤቱታ ማቅረባቸውም ተጠቁሟል፡፡

በተለይ ኮርፖሬሽኑ የስኳር አቅርቦቱን ካቋረጠ በኋላ መቼ እንደሚጀምር ባለመግለጹ፣ አማራጮችን ለመጠቀም እንኳን አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ኩባንያዎች ገልጸዋል፡፡

SOURCE
-Via:ethiopianreporter.com
-By:ዳዊት ታዬ
Original Link
http://www.ethiopianreporter.com